ቅዳሜ ነሐሴ 28 ቀን 2014 ሉናር ኢንተርናሽናል ኮሌጅ በመደበኛ መርሃ ግብር በኹለተኛ ዲግሪ ያስተማራቸውን 366 ተማሪዎች በስካይላይት ሆቴል በድምቀት አስመርቋል።

በምርቃቱ ዝግጅት ላይ የተመራቂ ተማሪዎችን ቤተሰቦችን ጨምሮ የኮሌጁ አስተዳደር፣ መምህራንና የክብር እንግዳዎች ተገኝተዋል።

የኮሌጁ ፕሬዝዳንት ታሪኩ አቶምሳ (ፒ.ኤች.ዲ.) ለ2014 ተመራቂዎች እንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈው፤ ተማሪዎቻቸው በቀጣይ ጉዟቸው ውጤታማ እንዲሁም ስኬታማ እንዲሆኑ ምኞትና ተስፋቸውን ገልፀዋል።

የኮሌጃችን ስኬት የሚመዘነው በተማሪዎች ስኬት ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ የኮሌጁም ዓላማ ተማሪዎቹ አገርን የሚያገለግሉ፣ በጎ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉ ማድረግ ነው ብለዋል።

ለተማሪዎች ባስተላለፉት መልዕክትም <<ለምርቃት መብቃት አንዱ ስኬት ቢሆንም በቀጣይ ለሚኖር ጉዞ መጀመሪያ ነው። በዚህ ጊዜ አገራችን ተወዳዳሪ ሆና በራሷ የምትተማመን አገር እንድትሆን መሥራት ይገባል።>> ሲሉ ለተመራቂ ተማሪዎች አደራ ብለዋል።

በንግግራቸውም ለክብር እንግዳዋ ጨምሮ ለተመራቂዎች ቤተሰቦች፣ ለኮሌጁ የአስተዳደር ሠራተኞ፣ ለኮሌጁ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት ምስጋና አቅርበዋል።

በዝግጅቱ ላይ በከፍተኛ ማዕረግ ለተመረቁ 31 ተማሪዎች ሽልማት ተሰጥቷል። እንዲሁም ኮሌጁ ለመጀመሪያ ጊዜ ባካሄደው ዓመቲዊ የተማሪዎች የምርምር አውደ ጥናት ላይ አሸናፊ ለሆኑ አምስት ጥናታዊ ፅሑፍ አቅራቢዎች የምስክር ወረቀት እና የገንዘብ ሽልማት ተበርክቷል።

በተጓዳኝ ኮሌጁ ለጥናትና ምርምር እንዲሁም ለማኅበረሰብ አገልግሎት ትኩረት እንደሚሰጥ የተገለፀ ሲሆን የተማሪዎች ጥናታዊ ሥራዎች በዓለምዓቀፍ የጥናት መፅሔቶች እንዲታተሙም የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል ተብሏል።

በምርቃት ዝግጅቱ ላይ ሦስት ተማሪዎች ከየትምህርት ክፍላቸው እጅግ ከፍተኛ ነጥብ በማምጣት የወርቅ ሜዳልያ ሲቀበሉ፤ ከሴት ተማሪዎች ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበች ተማሪም የዋንጫ ሽልማትን ከክብርት እንግዳዋ ተቀብላለች። በተጨማሪም ከሦስቱም የትምህርት ክፍሎች የላቀ ከፍተኛ ውጤት ላመጣ ተማሪም የዋንጫ ሽልማት ተበርክቷል።

በእለቱ የክብር እንግዳ የሆኑት የእናት ባንክ የኮርፖሬት አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ገነት ሐጎስ፤ ለተማሪዎች እንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ወ/ሮ ገነት ሓጎስ ባደረጉት ንግግር ኮሌጁ ተማሪዎች ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ በማበረታታ ፕሮጀክቶችን እንደሚቀርፅ ብሎም ማኅበራዊ ኃላፊነት በመወጣት እየወሰደ ያለውን ድርሻ አውስተዋል።

እናት ባንክም በተመሳሳይ በተለይ ሴቶች በሥራ ፈጠራ ራሳቸውን ችለው ከጥገኝነትና ከድህነት እንዲላቀቁ ለማድረግ በፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ የሚሠራውን ሥራና ማኅበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት የሄደውን ርቀትም አያይዘው አንስተዋል።

ከዚህ በመነሳት <<ሉናር ኢንተርናሽናል ኮሌጅ ጋር የርዕይ አጋርነት አለን>> ብለዋል። በቀጣይም በተማሪዎች የሚሠሩ ጥናቶችንና ፕሮጀክቶችን ወደ ሥራ በመቀየር በጋራ እንደሚሠሩ አስታውቀዋል።

በንግግራቸው ከራሳቸው የግል ተሞክሮና የሥራ ገጠመኝ በመነሳትና ምሳሌ በመጥቀስ፤ ተመራቂ ተማሪዎችም በቀጣይ በታማኝነትና በቅንነት እንዲያገለግሉ መልዕክታቸውን ከአደራ ጋር አስተላልፈዋል።

የእለቱ የክብርት እንግዳዋ በእለቱ የዋንጫ አሸናፊ ለሆኑ አንድ ወንድ እና አንድ ሴት ተመራቂዎች በእናት ባንክ ሥም፤ በባንኩ በሚከፈት አካውንት ለየአንዳንዳቸው የኻያ ሺሕ ብር የገንዘብ ስጦታን ለመስጠት ቃል ገብተዋል።

የሉናር ኢንተርናሽናል ኮሌጅ የ2014 ኹለተኛ ዲግሪ ተመራቂዎች ለኮሌጁ ኹለተኛ ዙር ተመራቂዎች ሲሆኑ፤ በቢዝነስ አድሚንስትሬሽን፣ በፋይናንስ እና ኢንቨስትመንት እንዲሁም በፕሮጀክት ማኔጅመንት ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው።

ኮሌጁ የማኅበራዊ ግዴታን ከመወጣት አንፃር የተለያዩና በርካታ ተግባራትን የሚያከናውን ሲሆን፤ ነሐሴ 17/2014 ከሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ ጋር <የሜሪ ጆይ ሱቆች> የተሰኘ ፕሮጀክት ለመደገፍ ከድርጅቱ ጋር የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሙን ይታወሳል።

Share your love

3 Comments

Leave a Reply